ወታደራዊ ድሮኖች

 ወታደራዊ ድሮኖች እና እያደገ የመጣው ግልጋሎታቸው

===================
ባለንበት ዘመን በድሮኖች አማካኝነት ስለሚከወን ጥቃት መስማት የተለመደ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ሆኖም የዛሬ 20 ዓመት ገደማ በወርሀ መስከረም የኒው ዮርክ መንትያ ህንፃዎች ላይ ከደረሰው ጥቃት ከአንድ ወር በኋላ ነበር አንድ የአሜሪካን አየር ኃይል አብራሪ ዘመናዊ ድሮንን ተጠቅሞ የግድያ ጥቃትን በመሰንዘር የመጀመሪያው ሰው የሆነው፡፡ ከዚህ በኋላ ግን በርካታ ርቀው ባሉ አብራሪዎች የሚንቀሳቀሱ አውሮፕላኖች (RPA) ተመራጭ የውጊያ መሳርያ ወደመሆን ተሸጋግረዋል፡፡ አሜሪካን እንኳን እንደምሳሌ ወስደን ብናይ ከአውሮፓውያኑ 2015 በኋላ በአፍጋኒስታን ውስጥ ብቻ ከ14 ሺህ በላይ የድሮን ጥቃቶችን አድርሳለች፡፡

ይህ መንግስታት በወታደራዊ ድሮኖች ላይ እያሳዩት የመጡት ከፍተኛ ፍላጎት ታድያ ሦስት አባይት ውጤቶችን አስከትሏል፡፡ የመጀመሪያው በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የወታደራዊ ድሮኖች ስርጭት መጨመሩ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ብዙዎቹ የዓለማችን ታላላቅ ብሎም በየአካባቢያቸው ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑት ሀገራት ድሮኖችን ለስለላና የአየር ላይ ምልከታ (ISR) አልያም ጥቃትን ለመሰንዘር እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ፡፡ ሁለተኛው ውጤት የመጀመሪያውን ተከትሎ የሚመጣ ነው፤ የድሮኖች መብዛትን ተከትሎ እነርሱን ማብረር እንዲችል ተደርጎ የሰለጠነ ወታደር የማፍራት ጉዳይ፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ድሮኖቹ በይበልጥ መሳርያን እየታጠቁ መምጣታቸው ነው፡፡

ምንም እንኳን ዘመናዊ ድሮኖችን ተጠቅሞ ጥቃት መሰንዘር ከተጀመረ ገና 20 ዓመታት ባያልፉትም ወታደራዊ ድሮኖች ግን የዘመኑ አዲስ ግኝቶች አይደሉም፡፡ እንዲያውም አውሮፕላን ከተፈጠረ ብዙም ሳይቆዩ ነው ድሮኖችም ገና በጠዋቱ በ1920 እና 30ዎቹ (እ.አ.አ) ከርቀት ሆኖ ጥቃትን ለመሰንዘር በማሰብ ወደ መድረኩ ብቅ ያሉት፡፡ ለምሳሌ ሚሳኤሎችም በሰው እየተመሩ ወደ ተልዕኮዋቸው የሚያመሩ ሲሆኑ ነገር ግን ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም የሚሰጡና ምንም አይነት ስለላን የማከናወን ብቃት የሌላቸው ናቸው፡፡ ሆኖም ዘመናዊ ወታደራዊ ድሮኖችን ለየት ከሚያደርጓቸው ውስጥ በመጀመሪያ አብራሪዎቻቸው ከደህንነት ከጥቃት የተጠበቁ መሆናቸው ነው፡፡ ሌላው እነዚህ ዘመናዊ ድሮኖች ኢላማቸውን ጠብቀው ጥቃት መሰንዘር የሚችሉ ስለሆኑ እንደ ሚሳኤል ካሉት አንፃር ጥቃት በሚፈፀምበት ቦታ ላይ አላስፈላጊ ተያያዥ ጉዳቶችን በተሻለ ያስቀራሉ፡፡ በተጨማሪም ለወታደሮቹ እና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎቹ ያለማቋረጥ መረጃን ይሰጣሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ድሮኖችን አስመልክቶ ከፍተኛ የሆነ የተሳሳተ ግንዛቤ ይታያል፤ በተለይም ድሮኖቹ እንዴት ይንቀሳቀሳሉ በሚለውና በአብራሪዎቹ ላይ፡፡ ድሮኖች የሚበሩት እነርሱን ለማብረር በማሰብ ተመልምለው በሰለጠኑ ወታደሮች አማካኝነት ነው፡፡ ታድያ እነዚህ አብራሪዎች እንደ ማንኛውም የአውሮፕላን አብራሪ ሁሉ ለሚከውኗቸው ተግባራት ኃላፊነትና ተጠያቂነት ቢኖርባቸውም በማህበረሰብም ሆነ በሌሎች ወታደሮች ዘንድ ግን በመልካም አይታዩም፡፡ ለምሳሌ ድሮኖችን ማብረር የቪዲዮ ጌሞችን ከመጫወት ጋር በማያያዝ የሚቀለድ ሲሆን አብራሪዎቹም ቢሆን ከሌሎች የአውሮፕላን አብራሪዎች አንፃር የስራ እድልን ሲከለከሉ ይታያል፡፡ ይህም የድሮን አብራሪዎች እጥረትን አስከትሏል፡፡ በሌላ መልኩ የድሮን አብራሪዎች ከአንድ አደጋ በኋላ የሚከሰት የጭንቀት በሽታ (Post traumatic stress disorder) ምልክት ቢታይባቸውም በወታደራዊ ተቋማቱ ጭምር የምር ተወስዶላቸው ህክምና ሲያገኙ አይስተዋልም፡፡

በሌላ መልኩ ጥቃት በሚፈፅሙበት ጊዜ ተያይዘው የተከሰቱ የንፁሀን ሞት በማህበረሰብ ዘንድ በመጥፎ እንዳይታዩ አድርጓቸዋል፡፡

Please #Share to your friend‼ ️
       ┈┈┈┈ •• ● ◉❖◉ ● •• ┈┈┈

            🦋SOT🦋
            

Post a Comment

0 Comments